የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አመሰራረት

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት እ.ኤ.አ ግንቦት 1976 በኢትዮጵያና በጀርመን መንግስት መካከል በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት የእጽዋት ጀነቲክ ሀብት ማዕከል (A Plant Genetics Resource Center) በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ተቋቋመ፡፡ ዋና ዓላማውም የሀገሪቱን የዕጽዋት ሀብቶች ከሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎች መጠበቅና የሰብል ምርቶችን ለማሻሻል ነበር፡፡ ቀጥሎም ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. አፕሪል 5/1994 54ኛዋ ሀገር ሆና የዓለም አቀፍ የብዝሀ ሕይወት ስምምነት ስትፈርም ይህንን ለማስፈፀም ይቻል ዘንድ በእጽዋት ላይ ብቻ ሲሰራ የቆየውን የእጽዋት ጀነቲክ ሀብት ማዕከል (PGRC/E) የእንስሳትና የደቂቅ አካላት እንዲጨምር ተደርጎ ሕይወታዊ ሀብት ጥበቃና ምርምር ኢንስቲትዩት (EBIR) በሚል በአዲስ መልክ ተመሰረተ፡፡ እ.ኤ.አ በ2004 በአዲስ መልክ ጥበቃ ላይ እንዲያተኩር ታስቦ የብዝሀ ሕይወት ጥበቃ ኢንስቲትዩት (EBI) በሚል ተቋቋመ፡፡ በመጨረሻም አሁን የያዘውን ቅርጽ በመያዝ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በሚል እኤአ በ2013 ተቋቋመ፡፡

ኃላፊትነት፣ ስልጣንና ተግባራት

ኢትዮጵያ የብዝሀ ሕይወት ሀብቶችን ለመንከባከብ በብሔራዊ ደረጃ ግልጽ ፖሊሲ ቀርጻለች፡፡ የእጽዋት ጀነቲክ ሀብት ማዕከል (A Plant Genetics Resource Center) በሚል ለእጽዋት ብቻ ትኩረት ሰጥታ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ከ1998 እ.ኤ.አ ጀምሮ በእጽዋት ላይ ብቻ ሲሰራ የቆየውን የእጽዋት ጀነቲክ ሀብት ጥበቃ ለሁሉም ዓይነት ማለትም ለእጽዋት፣ እንስሳትና ደቂቅ አካላት እንዲጨምር ተደርጎ ዘላቂ ተጠቃሚነትና ተያያዥ የማህበረሰብ እውቀቶችን መጠበቅንም አካቷል፡፡ ስርዓተ ምህዳርም የትኩረት ማዕከል እንዲሆን ተደርጓል፡፡ የሀገሪቱን የብዝሀ ሕይወት ሀብቶች በዘላቂነት የመጠበቅና የማስተዋወቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ዓለም አቀፍና የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በማዳበር የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል፡፡ አገሪቷ ለተቀበለቻቸው ብዝሀ ሕወትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ተጠሪ በመሆን ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ይዋዋላል፡፡

ራዕይ

በ2015 በብዝሀ ሕይወት ጥበቃ እና ዘለቄታዊ አጠቃቀም በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል መሆን

ተልዕኮ

የሀገራችን የብዝሀ ሕይወትና ተያያዥ ነባር ዕውቀቶችን በአግባቡ ማጥናት፣ አሳታፊ የጥበቃ ሥርዓትን መፍጠር፣ ማበልጸግ፣ አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነትን በማረጋገጥ ሀብቱ በዘላቂነት ለልማት እንዲውል ማመቻቸት

ዓላማ

የአገሪቱ ብዝሀ ሕይወት ሀብትና ተያያዥ የማህበረሰቦች እዉቀት በአግባቡ መጠበቃቸዉንና በዘላቂነት ጥቅም ላይ መዋላቸዉን እንዲሁም እነዚህን በመጠቀም ከሚገኘዉ ጥቅም አገሪቷና ማህበረሰቦቿ ፍትሀዊና ሚዛናዊ ድርሻ ማግኘታቸዉን ማረጋገጥ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት አደረጃጀት

ኢንስቲትዩቱ ስምንት የምርምር የሥራ ሂደቶች ማለትም፡- የአዝርዕትና ሆርቲካልቸር ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት፤ የእንስሳት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት፤ የደቂቅ አካላት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት፤ የደንና የግጦሽ መሬት ዕፅዋት ብዝሀ ሕይወት ዳይሬክቶሬት፤ የጀነቲክ ሀብት አርክቦትና ጥቅም ተጋሪነት ዳይሬክቶሬት፤ የምርምር፣ስርፀትና ፕሮጀክት ትግበራ ዳይሬክቶሬት፤ የቅርንጫፍ ማዕከላትና ባለድርሻ ሴክተሮች ዳይሬክቶሬት እና የስርዓተ-ምህዳር ዳይሬክቶሬት አሉት፡፡ በተጨማሪም ዘጠኝ አጋዥ የሥራ ሂደቶች ማለትም፡- የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት፤ የግዥ፣ፋይናንስና ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፤ የውስጥ ኦዲት ዳይሬክቶሬት፤ የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክቶሬት፤ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት፤ የኢንፎርሜሽንና ኮሙኑኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት፤ የሰው ሀብት ልማትና አስተዳደር ዳይሬክቶሬ፤ የለውጥና መልካም አስተዳደር ዳይሬክቶሬት፤ የሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና መከታተያ ዳይሬክቶሬት አሉት፡፡ ኢንስቲትዩቱ 7(ሰባት) የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት መቱ፣ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ መቀሌ፣ ጎባ፣ ባህርዳር እና አሶሳ ላይ አሉት፡፡ በተጨማሪም 2(ሁለት) የዕጽዋት አጸዶች በሻሸመኔ እና ጂማ ሲኖሩት በፍቼ አንድ የብዝሀ ሕይወት የጂን ባንክ አለው፡፡ ኢንስቲትዩቱ በዋና ዳይሬክተርና በም/ዋ/ዳይሬክተር የሚመራ ሲሆን የስራ አመራር ኮሚቴው ሁሉንም ዳይሬክቶሬቶች አቅፎ አመራር ይሰጣል፡፡